በአርሊን ጌትዝ
መስከረም 26፣ 2016 የእስራኤል እና የጋዛ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ፣ እስራኤል በዓለም ላይ ግንባር ቀደም የጋዜጠኞች አሳሪ አገር ሆና ብቅ እንዳለች የ2016 የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ (ሲፒጄ) ቆጠራ አሳይቷል። ከቻይና፣ ከማይናማር፣ ከቤላሩስ፣ ከሩሲያ እና ከቬትናም (እንደቅደም ተከተላቸው) ቀጥሎ፣ እስራኤል፣ ከኢራን እኩል የስድስተኛነትን ደረጃን ይዛለች።
በአጠቃላይ፣ ሲፒጄ ህዳር 21፣ 2016 ባደረገው ቆጠራ 320 ጋዜጠኞች እስር ላይ እንደነበሩ ዘግቧል። ይህ ቁጥር በ1985 በሲፒጄ ቆጠራ ከተጀመረ ወዲህ ከተመዘገበው ከፍተኛ ቁጥር የሁለተኛነትን ደረጃን ይዟል። ይህ ደግሞ፣ ስር የሰደደ የአምባገነንነት እና የመንግስታት የነፃነት ድምፆችን አፋኝነት የሚያሳይ አሳሳቢ መመዘኛ ነው። አንዳንድ መንግስታት፣ ከራሳቸው ድንበር አልፈው አንድ እርምጃ ወደ ፊት በመሄድ፣ ጋዜጠኞችን ለማስፈራራት እና ለማዋከብ፣ የድንበር ዘለል የጭቆና ዘዴ ይጠቀማሉ። ሞስኮ የተጠቀመችባቸው የማስፈራሪያ ድርጊቶች በሌሎች ሀገሮች የሚኖሩ የሩሲያ ጋዜጠኞች ላይ ተከታታይ የእስር ማዘዣዎችን ማውጣትን ያካትታሉ፤ ኢትዮጵያም በጎረቤቷ ጅቡቲ በስደት ይኖር የነበርን ጋዜጠኛ እንዲታሰር ካስደረገች በኋላ፣ በግድ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የሽብርተኝነት ክስ እንዲመሰረትበት አድርጋለች።
በተጨማሪም፣ የሲፒጄ ጥናት እንደሚያሳየው በቆጠራው ውስጥ ከተዘረዘሩት ክሶች ውስጥ፣ ከ65% (209) በላይ የሚሆኑት ታሳሪ ጋዜጠኞች፣ መንግስትን የሚተቹ የዜና ሽፋን በማቅረባቸው፣ የሃሰት ዜና ማሰራጨትና የሽብርተኝነት የመሳሰሉ የፀረ-መንግስት ወንጀሎች፣ በበቀል መልክ፣ ክስ እንዲመሰረትባቸው ያደርጋል። ከ67 የክስ መዝገቦች ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች የተከሰሱበት ጉዳይ፣ እስካሁን አልተነገራቸውም። ብዙውን ጊዜ፣ ያለምክንያት ጭካኔ የተሞላባቸው ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል፤ ብዙ ጊዜ የክስ ሂደቱን በማዛባት፣ ባለስልጣናት የቅድመ-ክስ እና የጋዜጠኞችን ቅድመ-ችሎት እስራት ሲያራዝሙ ይታያል፤ በጋዜጠኞች ጠበቆች ላይም በዓለም ዙሪያ የበቀል እርምጃ ሲወስድባቸው ይስተዋላል።
ሌሎች የ2016 ጥናት ቁልፍ ግኝቶች፤
ከሁሉም በከፋ መልኩ ብዙ ጋዜጠኞችን ያሰሩ ሀገሮች
ቆጠራው በተካሄደበት ቀን፣ ቻይና 44፣ ማይናማር 43፣ ቤላሩስ ደግሞ 28 ጋዜጠⶉችን በማሰር፣ ሶስቱ ሀገራት በወቅቱ እስር ላይ ከነበሩ ጋዜጠኞች መካከል ከአንድ ሦስተኛው በላይ (35.8%) የሚሆነውን ቁጥር ይዘው ነበር።
ቻይና ከረጅም አመታት ጀምሮ በዓለም ላይ ካሉት ግንባር ቀደም የጋዜጠኞች አሳሪዎች መካከል አንዷ ሆና ቆይታለች።ሀገሪቱ ላይ በሚደረግ ሳንሱር የተነሳ፣ የታሰሩትን ጋዜጠኞች ትክክለኛቁጥር ለማወቅ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው። ሆኖም፣ ቤጂንግ የምትፈፅመው የሚዲያ አፈና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተባባሰ መጥቷል፤ በ2012/13 የተካሄደው የሲፒጄ ቆጠራ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳሳየው፣ ከሆንግ ኮንግ የመጡ ጋዜጠኞች እስር ቤት ውስጥ ታጉረው ነበር። የሆንግ ኮንጉ እስራት የተፈፀመው፣ የአፍቃሪ-ዲሞክራሲ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ተከትሎ፣ ቤጂንግ ከባድ የብሄራዊ ደህንነት ህግ ከደነገገች በኋላ ነው። በወቅቱ ለእስር ከተዳረጉት ጋዜጠኞች መካከል፣ የበርካታዎቹ ጉዳዮች የፍርድ ሂደት ለረጅም ጊዜ ሲንከባለል ይታያል፤ ከእነዚህ መካከል፣ በአሁኑ ወቅት ስራ እንዲያቆም የተደረገው እና አፕል ዴይሊ የተሰኘው አፍቃሪ-ዴሞክራሲ ጋዜጣ መስራች ጂሚ ሌይ ጉዳይ አንዱ ነው። ሌይ ላይ የተመሰረተው የብሄራዊ ደህንነት ክስ የተጀመረው፣ ጋዜጠኛው 1,100 ያህል ቀናትን እስር ቤት ካሳለፈ በኋላ ነው። ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘም፣ በእድሜ ልክ ሊታሰር ይችላል።
ከዚህ በተጨማሪ፣ የቻይና ባለስልጣናት ጋዜጠኞችን ለማሰር የፀረ-መንግስት ክሶችን በመጠቀም ላይ ይገኛሉ፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ በ2016 በሲፒጄ የመረጃ ቋት ውስጥ ከተካተቱት አምስት አዳዲስ የቻይና ክሶች፣ ሦስቱ የሚያሳዩት፥ ጋዜጠኞቹ በስለላ፣ መነጣጠልን በማነሳሳት ወይንም የመንግስት ስልጣንን በማፍረስ የተከሰሱ መሆኑን ነው፤ ዚንጂያንግ፣ ቻይና በሰብአዊነት ላይ በምትፈጽመው ወንጀል የተከሰሰችበት ክልል ሲሆን፣ የተከሰሰችውም በአብዛኛው የሙስሊም ጎሳ በሆኑ የክልሉ ማህበረሰቦች ላይ በምትፈፅመው የጅምላ እስራት እና ከፍተኛ ጭቆና ነው። በ2016 ከታሰሩት 44 ጋዜጠኞች መካካል 19ኙ የዊገር ጋዜጠኞች ናቸው።
ከ2013 ጀምሮ በማይናማር እና ቤላሩስ ውስጥም የጋዜጠኞች ጭቆና ተባብሶ ቀጥሏል።
በየካቲት ወር 2013 ከተፈፀመው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት አንስቶ፣ ማይናማር ውስጥ የሀገሪቱ ነፃ ሚዲያ ወድሟል። በወቅቱ፣ ወታደራዊ ጁንታው ጋዜጠኞችን ለማሰር፣ የዜና ማሰራጫዎችን ለመዝጋት እና ጋዜጠኞችን በግዞት ለማፈናቀል በፍጥነት ተንቀሳቅሷል። ከሦስት ዓመታት ገደማ በኋላም፣ “የማነሳሳትን” እና “የውሸት ዜናን” ወንጀል ፈፅማችሗል በሚል ሰበብ፥ ጋዜጠኞችን ለመወንጀል በስፋት ጥቅም ላይ ለዋለው ፀረ-መንግስት ድንጋጌ ኢላማ ሆነው እንዲቀጥሉ ተደርጓል። በግንቦት ወር፣ የፎቶ ጋዜጠኛው ሳይ ዛው ታይኬ፥ በምዕራብ ማይናማር የተከሰተው እጅግ ከባድ አውሎ ንፋስ ያስከተለውን መዘዝ በመዘገብ ላይ እያለ ተይዞ ታስሯል፤ በማስከተልም፣ ህዝብን በመንግስት ላይ በማነሳሳት ወንጀል ተከሶ የ20 አመት እስራት ተፈርዶበታል–ይህም ከመፈንቅለ መንግስቱ ወዲህ በአንድ ጋዜጠኛ ላይ የተበየነ ረጅሙ የእስር ቅጣት ነው።
ቤላሩስ ውስጥ፣ ከ2013 አንስቶ ስራቸውን ስለሰሩ ብቻ በባለስልጣናት የሚታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ይህም የሆነው፣ የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ እንደገና በተመረጡበት አከራካሪ ምርጫ ሀገሪቱ በሕዝብ ተቃውሞ ስትናጥ በነበረበት ሁኔታ ነው። አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች (71% የሚሆኑት) የሚከሰሱት፣ በፀረ-መንግት ወንጀሎች ነው፤ ግማሽ ያህሉ፣ ለአምስት ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሚሆን የእስር ቅጣት ተበይኖባቸዋል።
የቤላሩስ ባለስልጣናት፣ ጋዜጠኞችን ለመቅጣት የ”አክራሪነት” ህጎችን አዘውትረው ይጠቀማሉ። ሲፒጄ በ2016 ባካሄደው የእስር ቆጠራ መሰረት፣ ከሰባት አዲስ የቤላሩስ እስረኞች መካከል፣ አምስቱ የፅንፈኛ ቡድኖችን በመፍጠር ወይም በፅንፈኝነት በመሳተፍ ወይም የፅንፈኛ እንቅስቃሴዎችን በማሳለጥ ተከሰዋል። (ሲፒጄም፣ አንድ ሌላ የቤላሩስ ጋዜጠኛ ተመሳሳይ ክስ እየቀረበበት መሆን አለመሆኑን እየመረመረ ይገኛል)። በስደት ላይ የሚገኘው የቤላሩስ የጋዜጠኞች ማህበር እንደገለፀው፣ ባለፉት ሁለት አመታት፣ ቢያንስ 19 የሚዲያ አውታሮች “ፅንፈኛ” በመባል ተፈርጀዋል።
አዳዲስ ለውጦች
በ2016 የእስር ቆጠራ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ሁለት ቁልፍ ለውጦች እስራኤል እና ኢራን ሲሆኑ፣ ኅዳር 21፣ 2016 እያንዳንዳቸው ቢያንስ 17 ጋዜጠኞችን ይዘው በማሰር፥ በአቻነት በስድስተኛ ደረጃ ላይ ተመዝግበው ይገኛሉ።
በሲፒጄ ዓመታዊ የጋዜጠኞች የእስር ቆጠራ ላይ እስራኤል ለበርካታ ጊዜ ተካታለች፤ ነገር ግን፣ ሲፒጄ የጋዜጠኞችን እስራት መዝገብ ከጀመረበት ከ1976 ወዲህ፣ ይህ ዓመት ከፍተኛው የፍልስጤም ጋዜጠኞች እስራት የተመዘገበት እና እስራኤልንም ከስድስቱ ዋና ዋና አሳሪዎች ተርታ ያሰለፈበት ወቅት ነው። ኅዳር 21፣ 2016 ሲፒጄ ካካሄደው ቆጠራ ጀምሮ፣ ሁሉም በእስራኤል ተይዘው እንደታሰሩ የሚታወቁት ጋዜጠኞች፣ መስከረም 26፣ 2016 የተቀሰቀሰውን የእስራኤል-ጋዛ ጦርነት ተከትሎ በተያዘው የዌስት ባንክ የፍልስጤም ግዛት ውስጥ የታሰሩ ናቸው። አብዛኛዎቹ ታስረው የሚገኙት፣ በአስተዳደራዊ እስራት ሲሆን፣ ይህም የእስራኤል ባለስልጣናት እስረኞችን ወደፊት ጥፋት የመፈጸም እቅድ አላቸው በሚል ጥርጣሬ ያለ ክስ አስሮ ለማቆየት ያስችላቸዋል።
እነዚህ ግልፅ ያልሆኑ (ያሰራር) ስርአቶች በጋዜጠኞች ላይ የሚነሱ ውንጀላዎችን ለማወቅ ጥረት ሲያደረጉ የነበሩ የሲፒጄ ተመራማሪዎች ስራ አዳጋች አድርጎባቸዋል፤ ይሁንና፣ ጋዜጠኞቹ የታሰሩት በማህበራዊ ድረ-ገጾች በሚለጠፏቸው መልዕክቶች የተነሳ መሆኑን በርካታ ቤተሰቦች ለሲፒጄ ነግረውታል። (ስለ እስራኤሉ የፍልስጤም ጋዜጠኞች እስራት እዚህ ያንብቡ )።
በአጠቃላይ፣ ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ እስራኤል ከ20 በላይ ጋዜጠኞችን አስራለች። ነገር ግን፣ ከህዳር 21፣ 2016 በፊት የተለቀቁት ወይም ከዚያ ቀን በኋላ የተያዙት ጋዜጠኞች ዝርዝር በ2015/2016ቱ ቆጠራ ውስጥ አልተካተቱም። (ሲፒጄ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ኣስመልክቶ በጣም በቅርቡ ያወጣቸውን አሃዞችን በተመለከተ እዚህ ይመልከቱ)።
በ22 ዓመቷ ማህሳ አሚኒ ሞት ሳቢያ የተቀሰቀሰውንና በሴቶች የተመራውን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደውን ተቃውሞ የዜና ሽፋን ማግኘቱን ተከትሎ፣ በአሁኑ ቆጠራ የተመዘገበው ቁጥር፣ በ2014 ከተመዘገበው እና እራንን ከሁሉ የበለጠች የጋዜጠኞች አሳሪ አስብሎ ካሰፈረጃት ጊዜ ወዲህ በእጅጉ ቀንሷል። በ2015 የእስር ቆጠራ ላይ ከተዘረዘሩት 62 ጋዜጠኞች መካከል፣ አብዛኛዎቹ በዋስ ተለቀው የተከሰሱበትን ጉዳይ ወይም የቅጣት ውሳኔያቸውን እየተጠባበቁ ነው። ይሁን እንጅ፣ በ2016 ሀገሪቱ ውስጥ የተመዘገበው ዝቅተኛ የታሳሪ ጋዜጠኞች ቁጥር፣ ኢራን በመገናኛ ብዙሃን ላይ እያደረሰች ያለውን የአፈና መጠን በምንም መልኩ አያመላክትም። ይልቁንስ፣ ባለሥልጣናቱ ስለሴቶች መብት ስላላቸው አመለካከት ሲጠየቁ የሰጡት ምላሽ፣ ታዋቂ ሴት ጋዜጠኞችን በመምረጥ ለእነሱ ምሳሌነት እንዲያገለግሉ በማድረግ ነው።
ከኀዳር 21 ቀን አንስቶ በኢራን ውስጥ ከታሰሩት 17 ጋዜጠኞች መካከል ስምንቱ ሴቶች ናቸው።
በመስከረም ወር 2015 ስለ አሚኒ ሞት ከዘገቡት የመጀመሪያዎቹ ጋዜጠኞች መካከል፣ ኒሎፋር ሃመዲ እና ኤላሄ መሀመዲ ይገኙበታል። እነዚህ ሁለት ሴት ጋዜጠኞች ከሰሩት ሪፖርት ጋር በተገናኘ፣ የፀረ- መንግስት የወንጀል ክስ ተመስረቶባቸው፣ እንደየቅደም ተከተላቸው የ13 እና 12 አመት የእስራት ቅጣት ተበይኖባቸው ለ16 ወራት ያህል በእስር ከቆዩ በኋላ፣ ጥር 5፣ 2014 በዋስ እንዲፈቱ ተፈቀዶላቸዋል–በመሃልም የኢራን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የይገባኝ አቤቱታቸውን ያይላቸዋል። የፍሪላንስ ጋዜጠኛዋ ቪዳ ራባኒ፣ ተቃውሞውን አስመልክታ በሰራችው ዘገባ የተነሳ፣ በሁለት ክሶች የ17 አመት እስራት ተፈርዶባት የመጀመሪያውን እስር በኤቪን እስር ቤት እያስተናገደች ትገኛለች።
ሩሲያም፣ ነፃ ዘገባን ለማፈን የምታደርገውን ጥረት አጠናክራለች። በየካቲት ወር 2014 ሩሲያ በዩክሬን ላይ የጀመረችውን የሙሉ በሙሉ ወረራ ተከትሎ፣ የሀገሪቱ ነፃ ሚዲያዎች አዝነው ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ሞስኮ ስደት ላይ ሆነው እየሰሩ ባሉ በርካታ ታዋቂ ጋዜጠኞች ላይ በሌሉበት የእስር ማዘዣ በማውጣት እና የእስር ቅጣት በመበየን፣ ከድንበሯ ባሻገር የጋዜጠኝነትን ስራ ለመወንጀል እየሞከረች ነው።
ከዚህ በተጨማሪ፣ ሩሲያ በእስር ቤቶቿ ውስጥ ያልተመጣጠነ የውጭ ጋዜጠኞች ቁጥር በእስር ይዛ ትገኛለች። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተካሄደው የታሳሪዎች ቆጠራ፣ በአጠቃላይ ከ17ት ታሳሪዎች ውስጥ 12ቱ የሀገር ውስጥ ያልሆኑ ታሳሪዎች የታሰሩት ሩሲያ ውሰጥ ነው። ከነዚህም ሁለቱ፣ ኢቫን ጌርሽኮቪች እና አልሱ ኩርማሼቫ፣ በቅድመ ችሎት በእስር ላይ የሚገኙ የአሜሪካ ዜጎች ናቸው። ከዩክሬን ከመጡት አስር ታሳሪ ጋዜጠኞች፥ አምስቱ የክሪሚያ ታታሮች ማለትም በ2006/2007 ሩሲያ መዝግባ በያዘችው መሰረት አብላጫው ሙስሊም የሆነ የክሬሚያ ልሳነ ምድር ተወላጅ ሲሆኑ፣ ከነዚህም አራቱ በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው ከ12 እስከ 19 ዓመት በሚደርስ የእስር ቅጣት ላይ ይገኛሉ። አሜት ሱሌይማኖቭ የተባለው አንደኛው ታሳሪ፣ የልብ፣ የሳምባ፣ የሆድ እና የመገጣጠሚያ ችግሮችን ጨምሮ በበርካታ የጤና እክሎች እየተሰቃየ ነው።
ጭካኔ እና የበቀል እርምጃ
ጋዜጠኞችን በማሰር እጅግ አስከፊ ታሪክ ባለባቸው ሀገራት፥ የእስር ቤቶቹ ሁኔታ አሰቃቂ ነው። በ2015 አጋማሽ ላይ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ያወጣው ብሄራዊ ዘገባ እንዳመለከተው፣ ቻይና፣ ማይናማር፣ ቤላሩስ፣ ሩሲያ እና ቬትናም ውስጥ የታሰሩ ጋዜጠኞች አካላዊ እና ወሲባዊ ጥቃት፣ መጨናነቅ፣ የምግብ እና የውሃ እጥረት እና በቂ ያልሆነ የህክምና ችግር ይገጥማቸዋል።
በ2015 በተደረገው የታሳሪዎች ቆጠራ፣ ከ320 ጋዜጠኞች መካከል፣ ቢያንስ 95ቱ ( 30% ያህሉ) የጤና ችግር እንዳለባቸው ይታወቃል። ብዙዎቹ፣ መድሃኒት ወይም ሃኪሞችን ማግኘት አይችሉም፤ ያም ሆኖ፣ ቤተሰቦቻቸው በታሰሩ ዘመዶቻቸው ላይ ሊደርስባቸው የሚችለውን የበቀል እርምጃ በመፍራት፣ ብዙውን ጊዜ ስለሁኔታወ መናገር አይፈልጉም። በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች የጤና እንክብካቤ፣ መድሃኒት እንደማያገኙ እና አንዳንዴም መሰረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶችን ማለትም እንደ ማሞቂያ፣ ሙቅ ውሃ እና ኤሌክትሪክ እንኳን የሚነፈጉባቻው በርካታ አጋጣሚዎች እንዳሉ፣ የሲፒጄ ጥናት ግኝት ያሳያል።
ለምሳሌ፣ የቬትናሟ ጋዜጠኛ ሁይንህ ቱክ ቪ የቬትናምን ባንዲራ አበላሽታለች በሚል ክስ ለሁለት አመት ከዘጠኝ ወር ያህል በእስር ላይ ትገኛለች። አባቷ ሁይን ንጎክ ቱአን በህዳር ወር 2016 ለሲፒጄ እንደተናገሩት፣ ልጃቸው ቪ፣ “ትሪከስፒድ ቫልቭ ሬጉሪጅቴሽን” በተሰኘ ከባድ የልብ ህመም እየተሰቃየች ትገኛለች። የዚህን ህመም (የሚፈውስ) መድሃኒት፣ እስር ቤቱ እንማያቀርብና ቤተሰቦቿም መድሃኒቱን ለመግዛት የገንዘብ አቅም የሌላቸው ከመሆኑም በላይ ከቤታቸው በ120 ማይል ርቀት ወደሚገኘው እስር ቤት በየጊዜው ተመላልሰው ሊያቀርቡላት አይችሉም።
በተጨማሪም፣ በቬትናም የእስር ቤት ኃላፊዎች ትራን ሁኒህ ዱይ ቱክ የተባለ እስረኛን ከእስር ቤቱ ካፍቴሪያ የሚገዛቸውን በፍጥነት ለማዘጋጀት የሚያስችለውን የሙቅ ውሃ አቅርቦት ከልክለውታል። ቱክ፣ “መንግስትን ለመገልበጥ በተደረጉ ተግባራት” ተሳትፈሃል በሚል ክስ፣ የ16 አመት እስራት ተፈርዶበት በእስር ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላም ተጨማሪ የአምስት አመት የቤት ውስጥ እስራት ይጠብቀዋል። ቱክ፣ እስር ቤት ውስጥ የሚታዩ መጥፎ ሁኔታዎች በመቃዎም ተደጋጋሚ የረሃብ አድማ አድርጓል፤ እንዲሁም፣ ፍትሃዊ ያልሆነ የምግብ አቅርቦትን በመቃወም ባለፈው መስከረም ወር ጀምሮ የእስር ቤት ምግብ መመገብ አቁሟል።
በ2010፣ ቱክ ለዓይን ህመም እንደተዳረገ፣ የቱክ ቤተሰብ አባላት ይናገራሉ፤ ይህም ሊሆን የቻለው፣ ቱክ የእስር ቤቱ ሃላፊዎች የታሰረበት ክፍል ውስጥ የኤሌክትሪክ አገልገሎት አዘውትረው በማቋረጥ ክፍሉ በጨለማ እንዲዋጥ በማድረጋቸው እና የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ለእስረኞች የተከለከሉ ናቸው በሚል ሰበብ ቤተሰቦቹ የሚያመጡለትን የባትሪ መብራቶች ለማቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው።
ሩሲያ ውስጥ፣ የስድስት አመት ከ11 ወራት እስራት የተፈረደባት ዩክሬናዊቷ የፍሪላንስ ጋዜጠኛ ኢሪና ዳኒሎቪች የግራ ጆሮዋን የመስማት ችሎታውን ያጣች ከመሆኗም በላይ በማያባራ ራስ ምታት እየተሰቃየች ቢሆንም፥ የህክምና አገልግሎት እንዳታገኝ ተነፍጋለች። የዳኒሎቪች አባት፣ “ኢሪና አይምሮዋን ለመሳት ቋፍ ላይ ናት”፣ በማለት ለሲፒጄ ተናግረዋል።
ቤላሩስ ውስጥ፣ ክሴኒያ ሉትስኪና በስምንት ዓመት የእስራት ዘመኗ፣ አንጎሏ ውስጥ እያደገ በመጣው እጢ የተነሳ እየተሰቃየች ቢሆንም፣ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እያገኘች አይደለም።
ከእስር ቤት የዘለለ ቅጣት
ብዙ ጋዜጠኞች የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ከተፈቱ በኋላም፣ ነጻነታቸውን የሚጋፋ ችግር ይገጥማቸዋል። ይህም በዕለት ተዕለት ኑሮአቸው ላይ ተጽኖ ከማሳደሩም በላይ፣ እነዚህ ሰዎች ድምፃቸውን እንዳያሰሙ፣ ለአፋኝ መንግስታት እድል ይሰጣቸዋል።
ለምሳሌ ያህል፣ ሩሲያ ውስጥ፣ አንድሬ ኖቫሾቭ የተሰኘ ጋዜጠኛ የስምንት ወር የእስር ቅጣቱን ከጨረሰ በኋላ ለአንድ አመት ያህል በጋዜጠኝነት እንዳይሰራ ታግዷል። ሙሉ የስድስት አመት እስራቱን ከጨረሰ በኋላ፣ በመጋቢት 2015 የተፈታው አሌክሳንደር ቫሎቭ በየሳምንቱ ለፖሊስ ሪፖርት እንዲያደርግ ግዴታ ውስጥ ከመግባቱም በላይ “በአስተዳደራዊ ቁጥጥር” ስር እንዲቆይ ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪም፣ ከጥቁር ባህር የሶቺ ከተማ ለሁለት አመታት ያህል እንዳይወጣ የተገደበ ሲሆን፣ በጋዜጠኝነት እንዳይሰራ የተጣለበት ክልከላን ከጨረሰ በኋላም እንኳን ለእንደሱ አይነቱ የመንግስት ተቺ ማንም ስራ መስጠት እንደማይፈልግ ለሲፒጄ ተናግሯል።
ቬትናም ውስጥ፣ አምስት ጋዜጠኞች፣ ማለትም ዶአን ኪን ጂያንግ፣ ትሩንግ ቻው ሁ ዳንህ፣ ኑጉየን ፎክ ትሩንግ ባኦ፣ ለ ዘ ታንግ እና ንጉየን ታን ናህ – አሁን ከጠፋው ነፃ ከሆነው ባኦ ሳች (ንፁህ ጋዜጣ) በፌስቡክ ላይ የተመሰረተ የዜና ማሰራጫ ጣቢያ ታግደዋል። በፀረ-መንግስት የወንጀል ክስ የእስር ጊዜያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ ለሶስት አመታት በጋዜጠኝነት እንዳይሰሩ ታግደዋል።
ኢራን ውስጥ፣ የአሚኒን ሞት የዘገበችው ናሲም ሶልታንቤይጊ በስርዓቱ ላይ ፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት እና በብሔራዊ ደህንነት ላይ በመመሳጠር የሶስት አመት ተኩል እስራት ከተፈረደባት በኋላ በተጨማሪ ለሁለት አመታት ከሀገር እንዳትወጣና ለሁለት አመት ደግሞ በማንኛውም የፖለቲካ ቡድን ወይም ጉባኤን እንዳትሳተፍ ተፈርዶባታል።
እስረኞች ወደ ፖለቲካ ተሀደሶ ካምፖች በሚላኩበት ወይም የቅጣት ፍርዳቸው ካበቃ በኋላም እንኳን በእስር ቤት በሚቆዩባት ሃገር ቻይና የዢንጂያንግ የዜና ድረ-ገጽ ዩጉርቢዝ መስራች ለነበረው እና እድሜ ልክ እስራት ለተፈረደበት ኢልሃም ቶህቲ ይሰሩ የነበሩ የተማሪዎች ቡድን አባላት እጣ ፈንታ እስካሁን ምን እንደሆነ አልታወቀም።
ግብፅም እንዲሁ የእስር ጊዜያቸውን ከጨረሱ በኋላ የጋዜጠኞችን እንቅስቃሴ የመገደብ ታሪክ አላት። ሻውካን በመባል የሚታወቀው የግብፁ የፎቶ ጋዜጠኛ እና የሲፒጄ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ተሸላሚ ማህሙድ አቡ ዘይድ በ2011 ከእስር ከተለቀቀ በኋላ ለአምስት ዓመታት ከዓለም አቀፍ ጉዞ ታግዶ ነበር።
ክልላዊ ጭቆና
በአንድ በተወሰነ ቀን ቅጽበታዊ በሆነ መልክ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን ቁጥር መመዘገብ የሁኔታውን ሙሉ ስዕል ሊያሳይ አለመቻሉ አያጠራጥርም። ያሳሪ ሀገሮች ደረጃ በፍጥነት ሊቀያያር ይችላል፤ እናም ሀገሮች ባንድ ወቅት ዝቅተኛ የታሳሪ ጋዜጠኞች ቁጥር ያላቸው መሆኑ በራሱ የተሻለ የፕሬስ ነፃነት እንዳለ አያመላክትም። ይህን በተመለከተ፣ እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱ ሀገራት እንደ ቱርክ፣ ግብፅ፣ ኢራን እና ሶሪያ ያሉ “የተሽከርካሪ በር” (“revolving door”) ፖሊሲ የሚያራምዱ መንግስታት ናቸው።
ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት
16 ጋዜጠኞችን አስራ የምትገኘው ኤርትራ፣ በዓለም ሰባተኛዋ፣ በአፍሪካ አህጉር ደግሞ የአንደኝነትን ደረጃ የያዘች ዋና የጋዜጠኞች አሳሪ ሀገር ናት። ኤርትራ ውስጥ ታስረው ከሚገኙት ጋዜጠኞች መካከል፣ በዓለም ዙሪያ በጣም ለረጅም ጊዜ በእስር ላይ በመቆየታቸው የሚታወቁ ጋዜጠኞችን ያካትታል፤ አንዳቸውም ክስ ተመስርቶባቸው አያውቅም።
ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት፣ ታህሳስ 21 ቀን 2016 የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር ወደ 47 ከፍ ብሏል፤ ይህ አሃዝ፣ በ2015 31 የነበረ ሲሆን፣ በ2014 ደግሞ 30 ነበር። ኢትዮጵያ (8)፣ ካሜሩን (6) ጋዜጠኞችን በማሰር በክልሉ የሁለተኛ እና የሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ቁጥር የሚያሳየው፣ የሀገሪቱ ሁኔታ ለመገናኛ ብዙሃን አመቺ አለመሆኑን ነው። ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን የእርስ በርስ ጦርነት የሚያስቆም የሰላም ስምምነት በ2014 የተፈረመ ቢሆንም፣ በአንዳንድ የሀገሪቱ ከፍሎች ኣለመረጋጋቱ እንደቀጠለ ነው፤ በሀገሪቱ የአማራ ክልል፣ በክልሉ ሚሊሻ እና በፌደራል ኃይሎች መካከል ግጭቱ ተጋግሎ ቀጥሏል። በ2016 በሲፒጄ ቆጠራ የተካተቱት ስምንቱም ጋዜጠኞች የታሰሩት ይህንኑ ግጭት ከዘገቡ በኋላ ነው።
የሲፒጄ መረጃ፣ በሴኔጋል፣ በዛምቢያ፣ በአንጎላ እና በማዳጋስካር በሚዲያ ላይ የደረሱ ጥቃቶችንም ያሳያል። አምስት ጋዜጠኞችን አስራ ያስቀመጠችው ሴኔጋል፣ ከዚህ ቀደም በሲፒጄ ቆጠራ የተካተተችው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው (በ2001 እና በ2015)።
የ2016 የሲፒጄ ቆጠራ እንደሚያሳየው፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ዛምቢያ፣ አንጎላ፣ ቡሩንዲ እና ናይጄሪያ እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ጋዜጠኛ አስረው ይገኛሉ። ለመጀመሪያ ጊዜ በሲፒጄ ቆጠራ የተካተተችው ማዳጋስካርም፣ አንድ ጋዜጠኛ አስራለች። ስታኒስ ቡጃኬራ ቲሺማላ በተሰኘው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋዜጠኛ የተመሰረቱት ክሶች መሰረት ያደረጉት የሀገሪቱን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ እና አዲሱን የዲጂታል ኮድና የፕሬስ ህግ ነው። እነዚህን ጥምር ህግጋት በመጠቀም፣ ባለሥልጣናት፣ ጋዜጠኞችን “የሐሰት ዜና” አጋርታችኋል፤ የኤሌክትሮኒክስ ዘዴን በመጠቀም መረጃ አሰራጭታችኋል ብለው ክስ ይመሰርቱባቸዋል፤ ያስሯቸዋል፤ ይህ ደግሞ፣ በየጊዜው እየታየ ያለውን የጋዜጠኝነት ስራን ወንጀል የማድረግን አሳሰቢ ሁኔታ ይበልጥ ግልፅ ያደርገዋል።
እስያ
እስያ፣ አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን ከፍተኛ ቁጥር የያዘ ክልል እነደሆነ ቀጥሏል። ከዋና ዋናዎቹ አሳሪ ሀገራት–ማለትም ከቻይና፣ ከማይናማር እና ከቬትናም ሌላ፣ ጋዜጠኞች በህንድ፣ በአፍጋኒስታን እና በፊሊፒንስ እስር ቤቶች ታሰረው ይገኛሉ።
ሰባት ጋዜጠኞችን አስራ የያዘችው ህንድ፣ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን (መከላከያ) ህግን (UAPA) እና የጃሙ እና ካሽሚር የህዝብ ደህንነት ህግን ጨምሮ የተለያዩ የደህንነት ህጎችን፣ ሚዲያዎችን ጸጥ ለማሰኘት ተጠቅማባቸዋለች።
አፍጋኒስታን እስከ ህዳር ወር ድረስ አንድ ጋዜጠኛ ብቻ በእስር ቤት ነበራት፤ ነገር ግን፣ ታሊባን በአፍጋኒስታን ጋዜጠኞች እና መገናኛ ብዙሃን ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ እስካሁን አልረገበም። ዓመቱን ሙሉ፣ ቢያንስ ሌሎች 16 ጋዜጠኞች ታስረዋል( በኋላም ተለቀዋል)–አንዳንዶቹን ጋዜጠኞች ታሊባን የሚከሳቸው በስደት ለሚገኙ ሚዲያዎች ትዘግባለችሁ በሚል ነው።
በፊሊፒንስ፣ በፕሬዚዳንት ፈርዲናንድ ማርኮስ ጁኒየር ዙሪያ ያለው የሚዲያ አያያዝ በአሰከፊነቱ ቀጥሏል፤ በጥቅሉ፣ ከርሳቸው በፊት በነበሩት መሪ ከነበረው ሁኔታ ኣንፃር ሲታይ፣ በጋዜጠኞች ላይ የሚታያው ግልፅ የሆነ የጠላትነት ስሜት አነስ ብሏል። በአንድ ወቅት የአካባቢው የፕሬስ ነፃነት ከለላ ተብላ በምትታወቀው የደቡብ ምስራቃዊቷ እስያ ሀገር ውስጥ በእስር ላይ የምትገኘዋ ጋዜጠኛ ፍሬንች ማይ ኩምፒዮ ብቻ ነች። ላለፉት አራት አመታት ያህል በእስር የቆየችው ኩምፒዮ፣ ለእስር የተዳረገችው፣ ጠበቆቿ እንደሚሉት፣ በህገ-ወጥ የመሳሪያ ዝውውር እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ ትደግፋለች በሚል የፈጠራ ክስ ተወንጅላ ነው።
አውሮፓ እና መካከለኛው እስያ
ከ7 እስከ 20 ዓመታት በሚደርስ የእስር ቅጣት፣ ሰባት ጋዜጠኞችን ያሰረችው በመካከለኛው እስያ የምትገኘዋ ታጂኪስታን፣ ጋዜጠኞችን በማሰር የመሪነት ስፍራውን ይዛ ቀጥላለች– ሁሉም ላይ የጥፋተኛነት ውሳኔ የተላለፈው ከ2015 መጀመሪያ አንስቶ ነው። በ2016 መጀመሪያ ላይ ሲፒጄ በሀገሪቱ ያደረገው ጉብኝት እንዳሳየው፣ በሀገሪቱ እየተላለፉ ያሉት ከባድ የቅጣት ውሳኔዎች፣ ወትሮም በመንግስት ጫና ተጎድቶ የነበረው የሚዲያ ድባብ፣ በፍረሃት ቆፈን እና በግል ሳንሱር የተነሳ ይበልጥ አስከፊ ሆኗል።
በየካቲት 2016 ሊካሄድ ከታቀደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቀደም ብሎ፣ በተደጋገሚ ከተፈፀሙት የጋዜጠኞች እስራት ጋር በተያያዘ፣ በ2016 መጀመሪያ ላይ የፕሬስ ነፃነት ሁኔታ፣ በአዘርባጃንም በፍጥነት እያሽቆለቆለ መጥቷል። ከህዳር 21 በፊት፣ አራት ጋዜጠኞች እና አንድ የሚዲያ ሰራተኛ ታስረዋል፤ ከዚያ ወዲህም ቢያንስ ሌሎች ሶስት ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገዋል። ኅዳር 21 ቀን ተይዘው የታሰሩት አራት ጋዜጠኞች ደግሞ፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ የሙስና ምርመራን በማድረግ የሚታወቀው የስመ ጥሩው የዜና አውታር፣ የአብዛስ ሚዲያ፣ ጋዜጠኞች ናቸው። ተይዘው የታሰሩትም፣ የአዘርባጃን ወታደራዊ ጣቢያ የሆነውን የናጎሮ-ካራበከን መልሶ መያዝን ተከትሎ ከመሆኑም በላይ፣ ወቅቱ በአዘርባጃን እና በምዕራባውያን መካከል ያለው ግንኙነት እያሽቆለቆለ የሄደበት ጊዜ ነበር፤ የአዘርባጃን ባለስልጣናት የአሜሪካን እና የአውሮፓ ኤምባሲዎችን እና ለጋሽ ድርጅቶችን ለዜና አውታሩ በህገ-ወጥ መንገድ የገንዘብ ድጋፍ አድርጋችኋል እያሉ በሚከሱበት ወቅት ነበር።
ሲፒጄ በ2015 አካሂዶት በነበረው ቆጠራ ወቅት ተመዘግበው ከነበሩት 40 ጋዜጠኞች ቁጥር ጋር ሲነፃፀር፣ ቱርክ ያሰረቻቸው 13 ጋዜጠኞች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል፤ ያም ሆኖ፣ በዓለም ደረጃ እረጅሙ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባት በእስር ላይ የምትገኘው ሴት ጋዜጠኛ ሃቲስ ዱማን አሁንም እንደታሰረች ነው፤ በእርሷ ላይ በድጋሚ የተደረገው የፍርድ አፈፃፀምም፣ በ2016ም ምንም አይነት ለውጥ አላመጣም። በተጨማሪም፣ ቀደም ሲል ከእስር ተፈተው የነበሩ ጋዜጠኞችም እሰካሁን ድረስ፣ በ2016ም በህግ ቁጥጥር ስር ናቸው፤ ለፖሊስ ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፤ ምናልባትም ከውጭ ጉዞ ሊታገዱ ይችላሉ፤ ወይም ጉዳያቸው በእንጥልጥል ቆይቶ ሌላ ምርመራ ሊካሄድባቸው ይችላል፤ ወይም ደግሞ እንደገና ለፍርድ ሊቀርቡ ይችላሉ። በ2016 መጀመሪያ ላይ፣ ሲፒጄ በቱርክ ያደረጋቸው መረጃን የማፈላለግ ጉብኝቶች እንዳሳዩት፣ በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞች ቁጥር ዝቅተኛ መሆን፣ በሀገሪቱ ያለውን የፕሬስ ነፃነት ድባብ መሻሻልን አያመለክትም።
መካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪካ
በ2016 በተደረገው ቆጠራ ግብፅ በመደበኛነት በዓለም ላይ ካሉ ዋና ዋና አሳሪዎች መካከል አንዷ በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከቱርክ እኩል (13 ጋዜጠኞችን በማሰር) የዘጠነኛ ደረጃን ይዛለች። ሳውዲ አረቢያ ደግሞ፣ 10 ጋዜጠኞችን አስራ፣ የአስረኛነትን ስፍራ ይዛለች።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሞሮኮ እና ኢራቅ ኩርዲስታን የሀሰት ዜና ማሰራጨትን፣ ሽብርተኝነትን እና የፀረ-መንግስት የወንጀል ክሶችን በጋዜጠኞች ላይ ለመመስረት በስፋት እየተጠቀሙባቸው ያሉ የክስ አይነቶች ናቸው። የግብፅ ባለስልጣናት የእስረኞችን ቅድመ-ችሎት በሁለት አመት የሚገድበውን ጊዜ ለማራዘም በሚያስቸላቸው (ማለትም ተጨማሪ ከሶችን በመመስረት) ህግ ዙሪያ አዘውትረው እየሰሩ ነው። ለዚህ እንደ ምሳሌ ተጠቃሽ የሚሆነው የፍሪላንስ ጋዜጠኛው የመሀመድ ሰኢድ ፋህሚ ጉዳይ ነው፤ በ2010 በሐሰት ዜና ማሰራጨት እና በሽብርተኝነት ክስ ተፈርዶበት ከታሰረ በኋላ፣ ከአራት አመት ተኩል የሚበልጥ የእስር ጊዜ አሳልፏል። በ2013 እና በ2014 ፣ ከእስር እንዲለቀቅ ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ አቃቤ ህግ ተጨማሪ ክሶችን ካከለ በኋላ የእስር ጊዜው እንዲራዘም ተደርጓል። የኳታር የዜና አውታር፥ የ“አልጀዚራ” ሲኒየር ካሜራማን ሙስጣፋ ሞሃመድ ሳድ ከ2012 ጀምሮ በሽብር እና በሀሰት ዜና ማሰራጨት ክስ ካይሮ ውሰጥ በቅድመ-ችሎት ታስሮ ይገኛል።
በ2016 እያንዳንዳቸው አምስት ጋዜጠኞችን በእስር የያዙት ባህሬን እና ሶሪያም ሆኑ እያንዳንዳቸው ሶስት፣ ሶስት እስረኞች ያሏቸው ሞሮኮ እና አልጄሪያ አዲስ እስራት አላስመዘገቡም። በኢራቅ ከታሰሩት አራቱ ጋዜጠኞች መካክል፣ አንደኛው አዲስ እስረኛ ሲሆን፣ ታስሮ የመጣውም ከኢራቅ ኩርዲስታን ነው። ቱኒዚያ ውስጥ በመስከረም ወር 2016 ዘብጥያ የወረደው ካሊፋ ጉሴሚ የብሔራዊ ደህንነት መረጃን በማጋለጥ ወንጀል ተከሶ ነው በአምስት ዓመት እስራት እንዲቀጣ የተፈረደበት። በዓመቱ አጋማሽ ችሎት የተሰየመው የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት፣ ቅጣቱን ከአንድ ዓመት ወደ አምስት ዓመታት ከፍ አድርጎበታል።
ላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን
በላቲን አሜሪካ እና በካሪቢያን አካባቢ፣ እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ጋዜጠኛ በማሰር በአንጻራዊነት ዝቅተኛ የታሳሪ ጋዜጠኞች ቁጥር ያስመዘገቡት ጓቲማላ፣ ኒካራጓ እና ኩባ፣ በክልሉ ባሉ ሌሎች ሀገራት እየታየ ያለውን የፕሬስ ነፃነትን የማዳከም አደጋ የሚፃረር ይመስላል፤ በተለይ በሆንዱራስ እና በኤልሳልቫዶር አያሌ ጋዜጠኞች ሀገር ለቀው እንዲሰደዱ ተገደዋል ።
ጓቲማላ ውሰጥ፣ ነጻ በሆኑ እና በምርመራ ጋዜጠኝነት በተሰማሩ የዜና አውታሮች ላይ የተጠኑ የጸረ-ፕሬስ ጥቃቶች በማካሄድ ሳንሱር ለማድረግ እና ፀጥ ለማሰኘት ሙከራ ተደርጓል። በሰኔ ወር 2015 ፣ የጓቲማላ ፍርድ ቤት በገንዘብ ማጭበርበር የተከሰሰውን የሆሴ ሩበን ሳሞራን የጥፋተኝነት ውሳኔ ሽሮ እና ጉዳዩ በድጋሚ በየካቲት ወር 2016 እንዲታይ ትእዛዝ ከሰጠለት በኋላም እንኳ፣ ጋዜጠኛው እስካሁን ድረስ በእስር ላይ ይገኛል። ሳሞራ፣ በሃምሌ ወር 2015 ከታሰረ ወዲህ፣ ስምንት ጊዜ ጠበቆችን ለመቀየር የተገደደ ሲሆን፣ አራት ጠበቆቹ በፍርድ ቤት ጥብቅና ስለቆሙለት የወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል። ኤልፔሪዮዲኮ የተባለው ነፃ ጋዜጣውም በመንግስት ግፊት በግንቦት ወር 2015 እንዲዘጋ ተደርጓል።
ኒካራጓ ውስጥ፣ የፍሪላንስ ዘጋቢው ቪክቶር ቲካይ፣ በፀረ-መንግስት እና በሐሰት የዜና ማሰራጨት ወንጀሎች ተከሶ፣ የስምንት ዓመታት እስራት ተፈረዶበት በእስር ላይ ይገኛል– እነዚህ ክሶች በተጠና መልክ፣ በኒካራጓ ነጻ ጋዜጠኞች ላይ የሚደረጉ ትንኮሳዎች፣ ማስፈራራቶች እና ውንጀላዎች ጋር የተሰናሰሉ ከመሆናቸውም በላይ፣ ፕሬዝደንት ዳንኤል ኦርቴጋ፣ ኒካራጓ ውስጥ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ለማፋን የሚያደረጉትን ጥረቶች ከፍ አድርገዋቸዋል።
የቆጠራ ዘዴ
የታሰሩ ጋዜጠኞች ቆጠራ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ጋዜጠኞችን ብቻ የሚመለከት ሲሆን የጠፉትን ወይም መንግስታዊ ባልሆኑ አካላት የታሰሩትን አይጨምርም። እንዲህ አይነቶቹ “የጠፉ” ወይም “የተጠለፉ” ተብለው ተመድበዋል።
ሲፒጄ ጋዜጠኞችን ሲገልፅ፣ በማንኛውም ሚዲያ ላይ ማለትም በሕትመት፣ ፎቶግራፎች፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን እና በኢንተርኔት ዜናን የሚዘግቡ ወይም በሕዝብ ጉዳዮች ላይ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች ናቸው ይላል። ሲፒጄ የሚያካሂደው ዓመታዊ የእስር ቤቶች ቆጠራ ከሥራቸው ጋር በተያያዘ መታሰራቸውን ያረጋገጠላቸውን ጋዜጠኞች ብቻ ያካትታል።
የሲፒጄ ዝርዝር በህዳር 21፣ 2016 እኩለ ለሊት ላይ የታሰሩት ሰዎች ቅጽበታዊ እይታ ነው። ይህ ዝርዝር፣ በዓመቱ ውስጥ የታሰሩትን እና የተፈቱትን አያሌ ጋዜጠኞችን አያካትትም። የእነሱ ዝርዝር መረጃ በ http://cpj-preprod.go-vip.net ላይ ይገኛል። ጋዜጠኞች እንደተለቀቁ ወይም በእስር ላይ እያሉ እንደሞቱ ድርጅቱ በተጨባጭ እስኪያረጋግጥ ድረስ በሲፒጄ ዝርዝር ውስጥ ይቆያሉ።
የመረጃ ቋት ዘገባ፤ በሰሚር አልሻሪፍ፣ አና ብራካህ፣ ቤህ ሊህ ዪ፣ ጆአን ቺርዋ፣ ሾን ክሪስፒን፣ ዶጃ ዳውድ፣ ኢግናሲዮ ዴልጋዶ ኩሌብራስ፣ ሶናሊ ዳዋን፣ ጀራልዳ ኢምባሎ፣ አይሪስ ሕሱ፣ ኒክ ሌዊስ፣ ኩናል ማጁምደር፣ መሀመድ ማንዱር፣ ሸሪፍ ማንሱር፣ ስኮት ማዬምባ፣ ሙቶኪ ሙሞ ፣ ሙሳ ንጎም ፣ ኦዝጉር ኦግሬት ፣ አንጄላ ኩንታል፣ ጆናታን ሮዘን፣ ጉልኖዛ ሰይድ፣ ሶራን ራሺድ፣ ዋሊላ ራህማኒ፣ ዬጊ ረዛያን፣ ዳና ቪልቼዝ፣ ክሪስቲና ዘሃር ናታሊ ግሪቫንያክ
የእስረኛ መለያዎችን የአርትኦት ስራ በአርሊን ጌትስ፣ ካቲ ጆንስ፣ ናኦሚ ዘቬሎፍ፣ ኬቲ ሚጊሮ፣ ሳራ ስፓይሰር፣ ጄኒፈር ደንሃም፣ ሱዛና ጎንዛሌስ እና ቶም ባርክሌይ